አዲስ አበባ, ሐምሌ 1 ቀን 2002 ዓ.ም (አዲስ አበባ)- የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቶሊክ ካህናት ማኅበር በኢትዮጵያ የካህናት ዓመት መዝጊያን በተመለከተ አገር አቀፍ ዓውደ ጥናት አካሄደ፡፡ 
የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቶሊክ ካህናት ማኅበር በኢትዮጵያ የካህናት ዓመትን መጠናቀቅ በማስመልከት ከኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ገዳማት የበላይ ኃላፊዎች ምክር ቤት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ዓውደ ጥናት ከሰኔ 29 እስከ ሐምሌ 1 2002 ዓ.ም በአዲስ አበባ ቅዱስ ፍራንሲስኮስ ነግር መለኮት ተቋም ተካሂዷል፡፡
ዓውደ ጥናቱ ሰኔ 29 ቀን ጠዋት ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ ከ150 በላይ ካህናት፣ ደናግልና
በርካታ ምእመናን በተገኙበት በቅዱስ ፍራንሲስኮስ ቁምስና ብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን ከመላው የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሀገረ ስብከቶች ብፁዓን ጳጳሳት ጋር በመሆን በመሩት ሥርዓተ ቅዳሴ ተከፍቷል፡፡

ብፁዕ አቡነ ብርሃነ የሱስ ስርዓተ ቅዳሴውን በመሩት ወቅት ባስተላለፉት ቃለ ምዕዳን ዛሬ ለዚህ ደስ የሚል ቀን ያደረሰን እግዚአብሄር የተመሰገነ ይሁን ካሉ በኋላ የካህናት ዓመት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የተጀመረውና የተጠናቀቀው በቅዱስ ልበኢየሱስ ዕለት መሆኑን አስታውሰው ካህን የፍቅር ስጦታ ነው ካህን ኢየሱስ ያፈቀረው እርሱም ደግሞ ኢየሱስን ስላፈቀረ ካህን በኢየሱስ ፍቅር ላይ የተመሰረተ የቤተክርስቲያን ስጦታ ነው፡፡ ቤተሰብ አሳድጎ ኮትኩቶ፣ ቤተክርስቲያንም በሚስትራት አንጻ በዘርዓ ክህነቶቿ አዘጋጅታ ለህዝብ የምታበረክተው የፍቅር ስጦታ ነው፡፡ ክርስቶስን ለማገልገልና ለማፍቀር ብቻ ሳይሆን ለዓለምም የተሰጠ የቤተክርስቲያን ዋና መሰረት ነው ብለዋል፡፡ አክለውም የክህናት ህይወት ከባድና በፈተናዊች የተከበበ ነው፡፡ ነገር ግን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቲዎስ እንደተናገረው እነዚያ ፈተናዎች እንዳሉ ሆነው ቢመችም ባይመችም በእግዚአብሄ ፍቅርና ጸጋ በመተማመን የወንጌልን ምስክርነት
በህይወታቸው መቀጠል አለባቸው ብለዋል፡፡
ከስርዓተ ቅዳሴው በማስከተል በቅዱስ ፍራንሲስኮስ የነገረ መለኮት ተቋም በተካሄደው ዓውደ ጥናት የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች የቀረቡ ሲሆን የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዓለም ዓቀፍ ሰነዶች፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ወቅታዊ ሐዋርያዊ ሥራ ሁኔታ፣ የካህናት መንፈሳዊነትና ሌሎችም በርካታ ርዕሶች በተለያዩ ምሁራን ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የብፁዕ ወቅዱስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ ሓዋርያዊ ሰላምታና ቡራኬ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ምዕመናን ብሔራዊ ምክር ቤት መልዕክቶችም ቀርበዋል፡፡

በቫቲካን ቅዱስ ጴጥሮስ ቤተክርስቲያን የተካሄደውን ዓለም ዓቀፍ የካህናት ዓመት ማጠናቀቂያ ላይ ታድመው የተመለሱ ካህናትም የክብረ በዓሉን ገጽታ ለዓውደጥናቱ ታዳሚዎች በመግለጽ ካህናት ሁላቸው በቅዱስነታቸው በተጠየቁት መሰረት ቃልኪዳናቸውን እንዲያድሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 
አውደ ጥናቱ ዛሬ ሐምሌ 1 ቀን 2002 ዓ.ም ከቀትር በኋላ የተናቀቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በክህነት አገልሎት 25ና 50 ዓመታት ያስቆጠሩ ካህናት የረጅም ዘመን የበጎ አገልግሎት መታሰቢያ የምስክር ወረቀት እንደሚሰጣቸው ታውቋል፡፡
|